1 ሳሙኤል 15:14-20 NASV

14 ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

15 ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።

16 ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው።ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት።

17 ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል።

18 እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር።

19 ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?”

20 ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ።