1 ሳሙኤል 19:1-7 NASV

1 ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር፣

2 እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ።

3 እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።”

4 ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል።

5 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?”

6 ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ።

7 ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ።