13 ሳኦልም፤ “ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በእኔ ላይ እንዲያምፅብኝና እንዲያደባብኝ፣ እንጀራና ሰይፍ በመስጠት፣ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ በመጠየቅ ከእሴይ ልጅ ጋር ለምን ዶለታችሁብኝ?” አለው።
14 አቢሜሌክም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ዐማች፣ የክብር ዘቦችህ አዛዥና በቤተ ሰብህ ዘንድ እጅግ የተከበረው ዳዊትን የመሰለ ታማኝ ከአገልጋዮችህ ሁሉ ማን አለ?
15 ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ስጠይቅስ ያ ቀን የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም፤ ይህን ጒዳይ በተመለከተ አገልጋይህ የሚያውቀው ምንም ነገር ስለሌለ ንጉሥ እኔን አገልጋዩን ወይም ከአባቴ ቤተ ሰብ ማንንም ጥፋተኛ አያድርግ።”
16 ንጉሡ ግን፣ “አቢሜሌክ ሆይ፤ አንተም የአባትህም ቤተ ሰብ በሙሉ በርግጥ ትሞታላችሁ” አለው።
17 ከዚያም ንጉሡ በአጠገቡ የቆሙትን ዘቦች፣ “እነዚህም የእግዚአብሔር ካህናት ከዳዊት ጋር ስላበሩ፣ ዳዊት መኰብለሉንም እያወቁ ስላልነገሩኝ ዙሩና ግደሏቸው” ሲል አዘዛቸው።የንጉሡ ሹማምት ግን እጃቸውን አንሥተው የእግዚአብሔርን ካህናት ለመምታት ፈቃደኞች አልሆኑም።
18 ንጉሡም ዶይቅን፣ “እንግዲያውስ አንተው ዙርና ካህናቱን ግደላቸው” ብሎ አዘዘው። ኤዶማዊው ዶይቅም ዞረና ገደላቸው። በዚያች ዕለት ሰማንያ አምስት የበፍታ ኤፉድ የለበሱ ካህናትን ገደለ።
19 የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ መታት፣ በዚያ የሚኖሩትንም ወንዶችንና ሴቶችን፣ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን፣ እንዲሁም በሬዎችንና አህያዎችን፣ በጎችንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጃቸው።