1 ሳሙኤል 23:18-24 NASV

18 ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ከዚያም ዮናታን ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊት ግን እዚያው ሖሬሽ ተቀመጠ።

19 የዚፍ ሰዎች ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ ዳዊት ከየሴሞን በስተ ደቡብ በኤኬላ ኰረብታ ላይ በሖሬሽ ምሽጎች ውስጥ በመካከላችን ተደብቆ የለምን?

20 አሁንም ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ደስ ባለህ ጊዜ ና እንጂ፣ እርሱን ለንጉሡ አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን።”

21 ሳኦል እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለእኔ ስለ ተቈረቈራችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤

22 አሁንም ሂዱና አጣሩ ዘወትር የት እንደሆነና በዚያ ያየውን ሰው ለይታችሁ ዕወቁ፤ እጅግ ተንኰለኛ መሆኑን ሰምቻለሁና።

23 የሚደበቅባቸውን ቦታዎች ሁሉ ካያችሁ በኋላ ግልጽ መረጃ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አብሬችሁ እሄዳለሁ፤ ብቻ በዚያ አገር ይገኝ እንጂ በይሁዳ ነገዶች ሁሉ መካከል ከገባበት ጒድጓድ ገብቼ አወጣዋለሁ።”

24 ስለዚህ ሰዎቹ ለመሄድ ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደ ዚፍ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሴሞን በስተ ደቡብ በዓረባ ውስጥ ባለው በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ።