1 ሳሙኤል 24:4-10 NASV

4 የዳዊት ሰዎችም ዳዊትን፣ “እግዚአብሔር፣ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” አሉት። ዳዊትም በልቡ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ማንም ሳያውቅ ቈርጦ ወሰደ።

5 ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቊረጡ ልቡ በሐዘን ተመታ።

6 ለሰዎቹም፣ “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና እግዚአብሔር የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ” አላቸው።

7 ዳዊት ሰዎቹን በዚህ ቃል ገሠጻቸው፤ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ከዋሻው ወጥቶ ሄደ።

8 ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፣ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤

9 ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፣ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ?

10 በዛሬው ዕለት በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ላይ እንደ ጣለህ እነሆ፤ በገዛ ዐይንህ አይተሃል፤ አንዳንዶች እንድገድልህ ገፋፍተውኝ ነበር፤ እኔ ግን፣ ‘እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ በማለት ራራሁልህ።