1 ሳሙኤል 25:25-31 NASV

25 ጌታዬ፣ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁም ነገር አይቍጠረው፤ ስሙ ራሱ ጅል ማለት ስለ ሆነ፣ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ጅልነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጐልማሶች አላየኋቸውም።

26 “ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤

27 አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጐልማሶች ይሰጥ።

28 ጌታዬ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለሚዋጋ እግዚአብሔርም ለጌታዬ ሥርወ መንግሥቱን በእርግጥ ለዘላለም የሚያጸናለት በመሆኑ፣ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ።

29 ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፣ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፣ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል።

30 እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣

31 ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን አስበኝ።”