1 ሳሙኤል 26:1-7 NASV

1 የዚፍ ሰዎች ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው፣ “እነሆ፤ ዳዊት በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ተደብቆአል” ብለው ነገሩት።

2 ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፤ ከእስራኤል የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ፣ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ።

3 ሳኦልም በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ላይ በመንገድ ዳር ሰፈረ፤ ዳዊት ግን በምድረ በዳ ነበር። ዳዊትም ሳኦል እዚያ ድረስ እንደ ተከተለው ባወቀ ጊዜ፣

4 ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ።

5 ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሰራዊቱ አለቃ፣ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ሳለ፣ ሰራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።

6 ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፣ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው።አቢሳም፣ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።

7 ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሰራዊቱ ወዳለበት ሄዱ። እነሆ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ጦሩም ራስጌው አጠገብ በመሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተው ነበር።