1 ሳሙኤል 26:14-20 NASV

14 ዳዊት ሰራዊቱንና የኔርን ልጅ አብኔርን፣ “አበኔር ሆይ፣ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ።አበኔርም፣ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።

15 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው ነህ? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለምንድን ነው?

16 ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”

17 ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤

18 በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?

19 አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፣ ቊርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።

20 አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”