1 ሳሙኤል 28:12-18 NASV

12 ሴትዮዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኽች፤ ሳኦልንም፣ “አንተ ሳኦል ሆነህ ሳለ፣ ለምን አታለልኸኝ?” አለችው።

13 ንጉሡም፣ “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት።ሴትዮዋም፣ “አንድ መንፈስ ከምድር ሲወጣ አያለሁ” አለችው።

14 እርሱም፣ “መልኩ ምን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት።እርሷም፣ “ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየወጣ ነው” አለችው።ሳኦልም ሴትዮዋ ያየችው ሳሙኤል መሆኑን ዐወቀ፤ በመሬትም ላይ ተደፍቶ እጅ ነሣ።

15 ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድ ነው?” አለው።ሳኦልም፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው።

16 ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ታዲያ እግዚአብሔር ከራቀህ፣ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ?

17 እግዚአብሔር በእኔ የተናገረውን አድርጎአል፤ እግዚአብሔር መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል።

18 ለእግዚአብሔር ስላልታዘዝህ፣ ታላቅ ቊጣውንም በአማሌቃውያን ላይ ስላል ፈጸምህ እግዚአብሔር ዛሬ ይህን አድርጎብሃል።