1 ሳሙኤል 29:4-10 NASV

4 የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን በአንኩስ ላይ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህን ሰው ወደዚያው ወደ ሰጠኸው ቦታ ይመለስ ዘንድ ስደደው፤ በውጊያው ጊዜ በእኛ ላይ ተመልሶ ጠላት እንዳይሆን፣ አብሮን ወደ ጦርነቱ መሄድ የለበትም፤ የእኛን ሰዎች ራስ ቈርጦ ካልወሰደ ከጌታው ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል?

5 በዘፈን እየተቀባበሉ፣‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ’ብለው የዘመሩለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?”

6 ስለዚህ አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ታማኝ ነህ፤ ወደ እኔ እዚህ ከመጣህበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም ጥፋት ያላገኘሁብህ ስለ ሆነ፣ አብረኸኝ ብትዘምት በበኩሌ ደስተኛ ነበርሁ፤ ነገር ግን ገዦቹ አልተቀበሉህም፤

7 እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ደስ የማያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”፤

8 ዳዊትም፣ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፣ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ስለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።

9 አንኩስም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፣ ‘አብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል።

10 አሁንም አብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማለዳ ተነሡ፤ በጥዋት ፀሓይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው።