1 ሳሙኤል 29:6-11 NASV

6 ስለዚህ አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ታማኝ ነህ፤ ወደ እኔ እዚህ ከመጣህበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም ጥፋት ያላገኘሁብህ ስለ ሆነ፣ አብረኸኝ ብትዘምት በበኩሌ ደስተኛ ነበርሁ፤ ነገር ግን ገዦቹ አልተቀበሉህም፤

7 እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ደስ የማያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”፤

8 ዳዊትም፣ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፣ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ስለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።

9 አንኩስም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፣ ‘አብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል።

10 አሁንም አብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማለዳ ተነሡ፤ በጥዋት ፀሓይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው።

11 ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ለመመለስ በማለዳ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።