1 ሳሙኤል 30:15-21 NASV

15 ዳዊትም፣ “ታዲያ ወራሪው ሰራዊት ወዳለበት መርተህ ታደርሰኛለህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው።

16 ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፣ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፣ ይጠጡና ይዘፍኑ፣ ይጨፍሩም ነበር።

17 ዳዊት፣ ከዚያች ዕለት ማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፣ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም።

18 ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፣ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ።

19 ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።

20 እንዲሁም ዳዊት የበጉን፣ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር።

21 ከዚያም ዳዊት፣ እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በቦሦር ወንዝ ቀርተው ወደ ነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው።