1 ሳሙኤል 30:19-25 NASV

19 ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።

20 እንዲሁም ዳዊት የበጉን፣ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር።

21 ከዚያም ዳዊት፣ እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በቦሦር ወንዝ ቀርተው ወደ ነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው።

22 ከዳዊት ተከታዮች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ ግን፣ “አብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ መሄድ ይችላል” አሉ።

23 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞቼ ሆይ፤ የጠበቀን፣ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር ይህን ማድረግ አይገባችሁም።

24 የምትሉትን ማን ይቀበላችኋል? ከጓዝ ጋር የቀረው ሰው ድርሻ ለጦርነት ከወጣው ሰው ድርሻ ጋር አይበላለጥም፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉ።”

25 ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ደንብና ሥርዐት አደረገው።