1 ሳሙኤል 31:1-7 NASV

1 በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያን ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ።

2 ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው ተከታተሉ፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ።

3 ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው እጅግ አቈሰሉት።

4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝ፣ እንዳያዋርዱኝ፣ አንተው ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው።ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ እምቢ አለው። ስለዚህ ሳኦል የራሱን ሰይፍ ወስዶ በላዩ ላይ ወደቀበት።

5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ባየ ጊዜ፣ እርሱም እንደዚሁ በሰይፉ ላይ ወድቆ አብሮት ሞተ።

6 ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ፣ አብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በዚያኑ ቀን ነበር።

7 በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።