1 ሳሙኤል 4:12-18 NASV

12 በዚያች ዕለት አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ፣ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ፣ ከጦሩ ሜዳ እየበረረ ወደ ሴሎ መጣ።

13 እዚያ እንደ ደረሰም፣ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ስለ ተጨነቀ፣ በመንገድ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወደ ከተማው ገብቶ የሆነውን ሁሉ ባወራ ጊዜ፣ ከተማው ሁሉ በጩኸት ተናወጠ።

14 ዔሊም ጩኸቱን በሰማ ጊዜ፣ “የምን ጩኸት ነው?” ሲል ጠየቀ።ሰውየውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው፤

15 ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ስለ ነበር ዐይኖቹ ደክመው ማየት ተስኖአቸው ነበር።

16 ሰውየውም ዔሊን፣ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው።ዔሊም፣ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ።

17 ወሬውን ያመጣውም ሰው፣ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሰራዊቱም ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኮአል” ብሎ መለሰለት።

18 ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፣ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፣ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበር።