1 ሳሙኤል 4:16-22 NASV

16 ሰውየውም ዔሊን፣ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው።ዔሊም፣ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ።

17 ወሬውን ያመጣውም ሰው፣ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሰራዊቱም ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኮአል” ብሎ መለሰለት።

18 ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፣ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፣ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበር።

19 በዚያን ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት፣ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት መማረክ፣ የዐማቷንና የባሏንም መሞት በሰማች ጊዜ ምጡ ስለ ጠናባት ተንበርክካ ወለደች።

20 ለመሞትም በምታጣጥርበት ጊዜ፣ በአጠገቧ የነበሩት ሴቶች፣ “አይዞሽ፤ ወንድ ልጅ ወልደሻልና በርቺ” አሏት። እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላዳመጠችም።

21 የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከ፣ ዐማቷና ባሏም ስለ ሞቱ፣ “ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ አለችው።

22 ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ተማርኮአልና ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” አለች።