14 ሠረገላውም ወደ ቤትሳሚስ ወደ ኢያሱ ዕርሻ መጥቶ በአንድ ትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን ዕንጨት ፈልጠው፣ ሁለቱን ላሞች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር አቀረቡ።
15 ሌዋውያኑም የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የወርቅ ዕቃዎቹን ከያዘው ሣጥን ጋር አውርደው በትልቁ ድንጋይ ላይ አኖሩ። በዚያችም ዕለት የቤትሳሚስ ሕዝብ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ።
16 አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦችም ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ በዚያኑ ዕለት ወደ አቃሮን ተመለሱ።
17 ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የላኳቸው የወርቅ ዕባጮች አንዱ ስለ አሽዶድ፣ አንዱ ስለ ጋዛ፣ አንዱ ስለ አስቀሎና፣ አንዱ ስለ ጌትና አንዱ ስለ አቃሮን የቀረቡ ናቸው፤
18 የወርቅ ዐይጦቹም ቊጥር፣ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች በሚያስተዳድሯቸው የተመሸጉ ከተሞችና ከእነዚህ ውጭ ባሉት መንደሮቻቸው ቊጥር ልክ ነው። በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ ዕርሻ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታቦት ያስቀመጡበት ያ ትልቅ ድንጋይ እስከ ዛሬ ምስክር ነው።
19 ነገር ግን እግዚአብሔር ከቤትሳሚስ ሰዎች ጥቂቱን መታ፤ ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና ከመካከላቸው ሰባ ሰዎችን ገደለ፤ እግዚአብሔር እጅግ ስለ መታቸውም ሕዝቡ አለቀሰ።
20 የቤትሳሚስም ሰዎች፣ “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ማን መቆም ይችላል? ታቦቱስ ከዚህ ወጥቶ ወደ ማን ይሂድ?” አሉ።