1 ሳሙኤል 7:6-12 NASV

6 እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ውሃ ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለት ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” ብለው ተናዘዙ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር።

7 እስራኤል በምጽጳ መሰብሰባቸውን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ የፍልስጥኤማውያን ገዦች ሊወጓቸው ወጡ፤ እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ፣ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ፤

8 ሳሙኤልንም፣ “አምላካችን እግዚአብሔር ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ወደ እርሱ መጸለይህን አታቋርጥ” አሉት።

9 ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ግልገል ወስዶ ሙሉ ለሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር አቀረበው፤ ስለ እስራኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም መለሰለት።

10 ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያሳርግበት ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት ቀረቡ። ይሁን እንጂ በዚያ ዕለት እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ ስላንጐዳጐ ደባቸው እጅግ ተሸበሩ፤ ድልም ተመተው ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ።

11 እስራኤላውያንም ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጥኤማውያንን በየመንገዱ እየገደሉ ከቤትካር በታች እስካለው ስፍራ ድረስ አሳደዷቸው።

12 ከዚህ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አቆመው፤ ስሙንም “እግዚአብሔር እስከ አሁን ድረስ ረድቶናል” ሲል “አቤንኤዘር” ብሎ ጠራው።