1 ቂስ የተባለ አንድ ታዋቂ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፣ የጽሮር ልጅ፣ የብኮራት ልጅ፣ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ ነበር።
2 ቂስም ከእስራኤል ልጆች መካከል በመልከ ቀናነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት፣ ቁመቱም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ፣ ሳኦል የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው።
3 በዚያም ጊዜ የሳኦል አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን፣ “ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልግ” አለው።
4 ስለዚህ በኰረብታማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኙም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። እንዲሁም በብንያም ግዛት በኩል ዐለፈ፤ ሆኖም አላገኟቸውም።
5 ወደ ጹፍ ግዛት በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፣ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፣ ና እንመለስ” አለው።
6 አገልጋዩ ግን፣ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት።
7 ሳኦልም አገልጋዩን፣ “መሄዱን እንሂድ፤ ነገር ግን ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቆአል። ለእግዚአብሔር ሰው የምናበረክተውም ስጦታ የለንም፤ ታዲያ ምን አለን?” አለው።