1 ሳሙኤል 9:10-16 NASV

10 ሳኦልም፣ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ።

11 በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፣ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፣ “ባለ ራእዩ እዚህ ነውን?” ሲሉ ጠየቁ።

12 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፣ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤

13 ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፣ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት፣ እርሱ እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡ መብላት አይጀምርም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።”

14 እነርሱም ወደ ከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ከተማዪቱም በመግባት ላይ ሳሉ፣ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ።

15 ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤

16 “ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቅባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሶአልና።”