1 ሳሙኤል 9:13-19 NASV

13 ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፣ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት፣ እርሱ እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡ መብላት አይጀምርም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።”

14 እነርሱም ወደ ከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ከተማዪቱም በመግባት ላይ ሳሉ፣ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ።

15 ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤

16 “ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቅባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሶአልና።”

17 ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ እግዚአብሔር፣ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው።

18 ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፣ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው።

19 ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጠዋት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ።