11 ስድስተኛው ዓታይ፣ ሰባተኛው ኢሊኤል፣
12 ስምንተኛው ዮሐናን፣ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፣
13 ዐሥረኛው ኤርምያስ፣ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ።
14 እነዚህ ጋዳውያን የጦር አዛዦች ነበሩ፣ ከእነርሱ ታናሽ የሆነው እንደ መቶ፣ ታላቅ የሆነው ደግሞ እንደ ሺህ አለቃ ይቈጠር ነበር።
15 በመጀመሪያው ወር የዮርዳኖስ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ ሳለ፣ ወንዙን ተሻግረው በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ሸለቆዎች ይኖሩ የነበሩትን ሁሉ ከዚያ ያባረሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ።
16 ሌሎች ከብንያምና ከይሁዳም ወገን የሆኑ ሰዎች ዳዊት ወደሚገኝበት ምሽግ መጡ።
17 ዳዊትም እነዚህን ሰዎች ሊቀበል ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ የመጣችሁት ልትረዱኝና በሰላም ከሆነ፣ ከእኔ ጋር እንድትሰለፉ ልቀበላችሁ ዝግጁ ነኝ፤ ነገር ግን እጄ ከበደል ንጹሕ ሆኖ ሳለ፣ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ፣ የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፤ ይፍረደውም”።