1 ዜና መዋዕል 16:2-8 NASV

2 ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ።

3 ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ጥፍጥፍ ተምር፣ ሙዳ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ ጥፍጥፍ ዘቢብ ሰጠ።

4 በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤

5 አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ ዖቤድኤዶም፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ።

6 እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ።

7 በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤

8 ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ፤ ስሙንም ጥሩ፤ለአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ንገሩ፤