1 ዜና መዋዕል 19:14-19 NASV

14 ከዚያም ኢዮአብና አብረውት ያሉት ወታደሮች ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሡ፤ ሶርያውያንም ከፊታቸው ሸሹ።

15 አሞናውያንም ሶርያውያን መሸሻቸውን ሲያዩ፣ እነርሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

16 ሶርያውያን በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ መልክተኞችን ልከው ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጡ፤ እነዚህንም የሚመራቸው የአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ ሾፋክ ነበረ።

17 ዳዊት ይህን ሲሰማ፣ እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ወደ ፊት በመገሥገሥም ከፊት ለፊታቸው የውጊያ መሥመሩን ያዘ። ዳዊትም ሶርያውያንን ጦርነት ለመግጠም ወታደሮቹን አሰለፈ፤ እነርሱም ተዋጉት።

18 ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ። ዳዊትም ሰባት ሺህ ሠረገለኞችና አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ገደለ። የሠራዊታቸው አዛዥ ሾፋክም በጦርነቱ ላይ ሞተ።

19 የአድርአዛርም ሹማምት በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ ከዳዊት ጋር ታረቁ፤ ገባሮቹም ሆኑ።ስለዚህ ሶርያውያን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኞች አልሆኑም።