1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን እንዲሁም በእስራኤል ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
2 እግዚአብሔር በሆሴዕ መናገር በጀመረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለ ሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” አለው።
3 ስለዚህ እርሱ የዴቤላይምን ሴት ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።
4 እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “በኢይዝራኤል ስለ ተፈጸመው ግድያ የኢዩን ቤት በቅርቡ ስለምቀጣና የእስራኤልንም መንግሥት እንዲያከትም ስለማደርግ፣ ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው።
5 በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ፣ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።”
6 ጎሜር እንደ ገና ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች፤ እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “ይቅር እላቸው ዘንድ ለእስራኤል ቤት ከእንግዲህ ስለማልራራላቸው፣ ስሟን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት።
7 ነገር ግን ለይሁዳ ቤት እራራለሁ፤ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶችና በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸው በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ።”