ሆሴዕ 14 NASV

በረከትን ለማግኘት ንስሓ መግባት

1 እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።

2 የምትሉትን ቃል ይዛችሁ፣ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤እንዲህም በሉት፤“ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣በምሕረትህ ተቀበለን።

3 አሦር ሊያድነን አይችልም፤በጦር ፈረሶችም ላይ አንቀመጥም፤ከእንግዲህም የገዛ እጆቻችን የሠሯቸውን፣‘አምላኮቻችን’ አንላቸውም፤ድኻ አደጉ ከአንተ ርኅራኄ ያገኛልና።”

4 “እኔ ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤እንዲሁ እወዳቸዋለሁ፤ቊጣዬ ከእነርሱ ተመልሶአልና።

5 እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤እንደ ውብ አበባ ያብባል፤እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣ሥር ይሰዳል፤

6 ቅርንጫፉ ያድጋል፤ውበቱ እንደ ወይራ ዛፍ፣ሽታውም እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይሆናል።

7 ሰዎች እንደ ገና ከጥላው በታች ያርፋሉ፤እርሱም እንደ እህል ይለመልማል፤እንደ ወይን ተክል ያብባል፤ዝናውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ይወጣል።

8 ኤፍሬም ሆይ፤ ከእንግዲህ ከጣዖት ጋርምን ጒዳይ አለኝ?የምሰማህና የምጠነቀቅልህ እኔ ነኝ፤እኔ እንደለመለመ የጥድ ዛፍ ነኝ፤ፍሬያማነትህም ከእኔ የተነሣ ነው።”

9 ጥበበኛ የሆነ እነዚህን ነገሮች ያስተውላል፤አስተዋይም እነዚህን ነገሮች ይረዳል። የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነውና፤ጻድቃን ይሄዱበታል፤ዐመፀኞች ግን ይሰናከሉበታል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14