ሰቆቃወ 1:9-15 NASV

9 ርኵሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤የሚያጽናናትም አልነበረም፤“እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬንተመልከት፤ጠላት ድል አድርጎአልና!”

10 በሀብቷ ሁሉ ላይ፣ጠላት እጁን ዘረጋ፤ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ፣የከለከልሀቸው፣ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች።

11 እንጀራ በመፈለግ፣ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤በሕይወት ለመኖር፣የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤እኔ ተዋርጃለሁና።”

12 “እናንት መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን?ተመልከቱ፤ እዩም፤በጽኑ ቍጣው ቀን፣ እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣በእኔ ላይ የደረሰውን፣የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?

13 “ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤ወደ ኋላም ጣለኝ፤ቀኑን ሙሉ በማድከም፣ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ።

14 “ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤ኀይሌንም አዳከመ፤ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ።

15 “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ፣እግዚአብሔር ተቃወመ፤ጒልማሶቼን ለማድቀቅ፣ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ፤ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።