ሶፎንያስ 1:1-7 NASV

1 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፣ ወደ አማርያ ልጅ፣ ወደ ጎዶልያስ ልጅ፣ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

2 “ማንኛውንም ነገር፣ከምድር ገጽ አጠፋለሁ”ይላል እግዚአብሔር።

3 “ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤የሰማይን ወፎች፣የባሕርንም ዓሦች አጠፋለሁ፤ሰውን ከምድር ገጽ በማስወግድበት ጊዜ፣ክፉዎች የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ”ይላል እግዚአብሔር።

4 “እጄን በይሁዳ፣በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አነሣለሁ፤የበኣልን ትሩፍ፣የጣዖታቱንና የአመንዝራ ካህናቱን ስም ሁሉ ከዚህ ስፍራ አጠፋለሁ፤

5 የሰማይን ሰራዊት ለማምለክ፣በሰገነት ላይ ወጥተው የሚሰግዱትን፣ ለእግዚአብሔር እየሰገዱ፣ በስሙም እየማሉ፣በሚልኮምም ደግሞ የሚምሉትን፣

6 እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ የሚመለሱትን፣እግዚአብሔርን የማይፈልጉትን፣ እንዲረዳቸውም የማይጠይቁትን አጠፋለሁ።

7 በልዑል እግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ፤የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና። እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቶአል፤የጠራቸውንም ቀድሶአል።