ሶፎንያስ

ምዕራፎች 1

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፣ ወደ አማርያ ልጅ፣ ወደ ጎዶልያስ ልጅ፣ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

ስለሚመጣው ጥፋት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

2“ማንኛውንም ነገር፣ከምድር ገጽ አጠፋለሁ”ይላል እግዚአብሔር። 3“ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤የሰማይን ወፎች፣የባሕርንም ዓሦች አጠፋለሁ፤ሰውን ከምድር ገጽ በማስወግድበት ጊዜ፣ክፉዎች የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ”ይላል እግዚአብሔር።

በይሁዳ ላይ የተነገረ ጥፋት

4“እጄን በይሁዳ፣በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አነሣለሁ፤የበኣልን ትሩፍ፣የጣዖታቱንና የአመንዝራ ካህናቱን ስም ሁሉ ከዚህ ስፍራ አጠፋለሁ፤ 5የሰማይን ሰራዊት ለማምለክ፣በሰገነት ላይ ወጥተው የሚሰግዱትን፣ ለእግዚአብሔር እየሰገዱ፣ በስሙም እየማሉ፣በሚልኮምም ደግሞ የሚምሉትን፣ 6 እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ የሚመለሱትን፣እግዚአብሔርን የማይፈልጉትን፣ እንዲረዳቸውም የማይጠይቁትን አጠፋለሁ። 7በልዑል እግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ፤የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና። እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቶአል፤የጠራቸውንም ቀድሶአል። 8 በእግዚአብሔር የመሥዋዕት ቀን፣መሳፍንቱንና የንጉሡን ልጆች፣እንግዳ ልብስ የሚለብሱትን ሁሉ እቀጣለሁ። 9በዚያን ቀን፣በመድረኩ ላይ የሚዘሉትን ሁሉ፣የአማልክቶቻቸውን ቤት፣በዐመፅና በማጭበርበር የሚሞሉትን እቀጣለሁ። 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በዚያ ቀን ‘ከዓሣ በር’ ጩኸትበሁለተኛው አደባባይ ዋይታ፣ከኰረብቶችም ታላቅ ሽብር ይሰማል። 11እናንት በመክቴሽ ገበያ የምትኖሩ ዋይ በሉ፤ነጋዴዎቻችሁ ሁሉ ይደመሰሳሉ፤በብር የሚነግዱትም ሁሉ ይሞታሉ። 12በዚያ ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤ተንደላቀው የሚኖሩትን፣በዝቃጩ ላይ እንደ ቀረ የወይን ጠጅ የሆኑትን፣‘ክፉም ይሁን መልካም፣ እግዚአብሔር ምንም አያደርግም’ የሚሉትን ቸልተኞች እቀጣለሁ። 13ሀብታቸው ይዘረፋል፤ቤታቸው ይፈራርሳል፤ቤቶች ይሠራሉ፤ነገር ግን አይኖሩባቸውም፤ወይን ይተክላሉ፤ጠጁን ግን አይጠጡም።

ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን

14“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል፤ በእግዚአብሔር ቀን የሚሰማው ልቅሶ መራራ ነው፤በዚያ ጦረኛውም ምርር ብሎ ይጮኻል፤ 15ያ ቀን የመዓት ቀን፣የመከራና የጭንቀት ቀን፣የሁከትና የጥፋት ቀን፣የጨለማና የጭጋግ ቀን፣የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፤ 16ያ ቀን በተመሸጉ ከተሞችና፣በረጃጅም ግንቦች ላይ፣የመለከት ድምፅና የጦርነት ጩኸት የሚሰማበት ቀን ይሆናል። 17እንደ ዕውር እንዲራመዱ፣በሰዎች ላይ ጭንቀት አመጣባቸዋለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአትን ሠርተዋልና።ደማቸው እንደ ትቢያ፣ሥጋቸውም እንደ ጒድፍ ይጣላል። 18 በእግዚአብሔር የቊጣ ቀን፣ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው፣ሊያድናቸው አይችልም፤መላዪቱ ምድር፣በቅናቱ ትበላለች፤በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ፣ድንገተኛ ፍጻሜ ያመጣባቸዋልና።”

ምዕራፎች