ነህምያ 1:1-7 NASV

1 የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል፤በሃያኛው ዓመት ካሴሉ በተባለው ወር በሱሳ ግንብ ሳለሁ፣

2 ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው አናኒ፣ ከሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋር ከይሁዳ መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎችና ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው።

3 እነርሱም፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሶአል፤ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።

4 ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አያሌ ቀናት ዐዘንሁ፤ ጾምሁ፤ ጸለይሁም።

5 ከዚያም እንዲህ አልሁ፤“ለሚወዱህና ትእዛዝህን ለሚያከብሩ የፍቅርህን ቃል ኪዳን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፣ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤

6 ባሪያህ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤል ሕዝብ ቀንና ሌሊት በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ይንቃ፤ ዐይንህም ይከፈት። እኔንና የአባቴን ቤት ጨምሮ እኛ እስራኤላውያን አንተን በመበደል የሠራነውን ኀጢአት እናዘዛለሁ።

7 በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሥራ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ የሰጠኸውን ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ አልጠበቅንም።