ነህምያ 10:33-39 NASV

33 ይህም በጠረጴዛው ላይ ለሚቀርበው ገጸ ኅብስት፣ ዘወትር ለሚቀርበው የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ በሰንበት፣ በወር መባቻና በተደነገጉ በዓላት ለሚቀርበው መሥዋዕት፣ ለተቀደሱ መባዎች፣ ለእስራኤል ስርየት ለሚቀርበው የኀጢአት መሥዋዕትና ለአምላካችን ቤት ሥራ ሁሉ የሚውል ነው።

34 “እኛ፣ ማለት ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና ሕዝቡ በየዓመቱ በተወሰነው ጊዜ በሕጉ እንደ ተጻፈው፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚነደውን ዕንጨት የእያንዳንዳችን ቤተ ሰብ መቼ ወደ አምላካችን ቤት ማምጣት እንዳለበት ለመወሰን ዕጣ ተጣጣልን።

35 “የሰብላችንንና የእያንዳንዱን ዛፍ ፍሬ በኵራትም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማምጣት ቃል እንገባለን።

36 “እንዲሁም በሕጉ እንደ ተጻፈው የወንድ ልጆቻችንንና፣ የቀንድ ከብቶቻችንን፣ የመንጋዎቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን በኵራት ወደ አምላካችን ቤት፣ ወደሚያገለግሉትም ካህናት እናመጣለን።

37 “ከዚህም በላይ የቡሆአችንን፣ የእህል ቍርባናችንን፣ የዛፎቻችንን ፍሬ ሁሉ፣ አዲሱን የወይን ጠጃችንንና የዘይታችንን በኵራት ወደ ካህናቱ፣ ወደ አምላካችን ቤት ዕቃ ቤቶች እናመጣለን። እኛ በምንሠራባቸው ከተሞች ሁሉ ያለውን ዐሥራት የሚሰበስቡት ሌዋውያን ስለሆኑ፣ የሰብላችንን ዐሥራት ወደ ሌዋውያኑ እናመጣለን።

38 ዐሥራቱን በሚቀበሉበት ጊዜም ከአሮን ዘር የተወለደው ካህን ከሌዋውያኑ ጋር አብሮ ይገኛል፤ ሌዋውያኑም የዐሥራቱን አንድ ዐሥረኛ ወደ አምላካችን ቤት፣ ወደ ዕቃ ማከማቻ ክፍሎች ያመጡታል።

39 የእስራኤል ሕዝብና ሌዋውያኑ ጭምር፣ ከእህሉ፣ ከዐዲሱ ወይን ጠጅና ከዘይቱ ያዋጡትን፣ የመቅደሱ ዕቃዎች ወደሚቀመጡባቸው፣ አገልጋይ ካህናት፣ በር ጠባቂዎቹና መዘምራኑ ወደሚያርፉባቸው ዕቃ ቤቶች ያምጡ።“እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም።”