ነህምያ 12:36-42 NASV

36 ወንድሞቹ ሸማያ፣ ኤዝርኤል፣ ሚላላይ፣ ጊላላይ፣ መዓይ፣ ናትናኤል፣ ይሁዳና አናኒም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የዜማ መሣሪያዎቹን ይዘው ሄዱ፤ ሰልፉን የሚመራውም ጸሓፊው ዕዝራ ነበረ።

37 “ከምንጭ በር” ተነሥተው በቀጥታ ወደ “ዳዊት ከተማ” ደረጃዎች ወጡ፤ ከዚያም በቅጥሩ መውጫ በኩል አድርገው ከዳዊት ቤት በላይ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ “ውሃ በር” ሄዱ።

38 ሁለተኛው የመዘምራን ቡድን በስተ ግራ በኩል ሄደ፤ እኔም ከከፊሉ ሕዝብ ጋር ሆኜ በቅጥሩ ግንብ ላይ፣ የእቶኑን ግንብ በማለፍ እስከ ሰፊው ቅጥር ተከተልኋቸው፤

39 ከዚያም ከኤፍሬም በር በላይ፣ በአሮጌ በር፣ በዓሣ በር፣ በሐናንኤል ግንብ፣ በመቶዎቹ ግንብ አልፌ እስከ “በጎች በር” ድረስ ተከተልኋቸው። እነርሱም “በዘበኞች በር” አጠገብ ሲደርሱ ቆሙ።

40 ቀጥሎም ምስጋና ያቀረቡት ሁለቱ የመዘምራን ቡድኖች፣ በእግዚአብሔር ቤት ቦታቸውን ያዙ፤ እኔም ከግማሾቹ ሹማምት ጋር ቦታዬን ያዝሁ፤

41 እንደዚሁም ካህናቱ ኤልያቄም፣ መዕሤያ፣ ሚንያሚን፣ ሚካያ፣ ኤልዮዔናይ፣ ዘካርያስና ሐናንያ መለከታቸውን ይዘው፣

42 መዕሤያ፣ ሸማያ፣ አልዓዛር፣ ኦዚ፣ ይሆሐናን፣ መልክያ፣ ኤላምና ኤጽር ቦታቸውን ያዙ፤ መዘምራኑ በይዝረሕያ መሪነት ዘመሩ።