ነህምያ 3:4-10 NASV

4 የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤

5 የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሐ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንቶቻቸው ግን በተቈጣ ጣሪ አሠሪዎቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም።

6 አሮጌውን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

7 ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር።

8 ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐር ሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም “ሰፊው ቅጥር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ።

9 ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሆር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ።

10 የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ።