ነህምያ 4:10-16 NASV

10 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጒልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ።

11 ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ።

12 ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው፣ “እናንተ የትም ቦታ ብትሆኑ፣ እኛን ማጥቃታቸው አይቀርም!” በማለት ዐሥር ጊዜ ደጋግመው ነገሩን።

13 ስለዚህ ከቅጥሩ በስተ ኋላ በሚገኙ ግልጽ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን እንደ ያዙ በየቤተ ሰባቸው በመመደብ ቦታቸውን እንዲይዙ አደረግሁ።

14 ነገሩን በጥሞና ከተመለከትሁ በኋላ መኳንንቱን፣ ሹማምቱንና የቀረውን ሕዝብ፣ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን እግዚአብሔርን አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤት ንብረታችሁ ተዋጉ” አልኋቸው።

15 አድማቸውን እንዳወቅንባቸውና እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን ከንቱ እንዳደረገባቸው ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችን ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችንም ወደየሥራችን ተመለስን።

16 ከዚያን ቀን ጀምሮ ከሰዎቼ እኩሌቶቹ ሥራውን ሠሩ፤ የቀሩት ደግሞ ጋሻና ጦር፣ ቀስትና ጥሩር ይዘው ነበር። የጦር አለቆች ከመላው የይሁዳ ሕዝብ በስተ ኋላ ቆሙ፤