ነህምያ 4:17-23 NASV

17 እነርሱም ቅጥሩን ይገነቡ ነበር፤ ዕቃ የሚሸከሙት በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር፤

18 እያንዳንዱም ግንበኛ ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ መለከት የሚነፋው ሰው ግን ከእኔ አይለይም ነበር።

19 ከዚያም ለመኳንንቱ፣ ለሹማምቱና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ አልሁ፤ “ሥራው ታላቅ ነው፤ ብዙም ነው፤ እርስ በርሳችን በቅጥሩ ላይ እጅግ ተራርቀናል፤

20 የመለከት ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።”

21 ስለዚህ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ሰዎች ጦራቸውን እንደ ያዙ ሥራውን ቀጠልን።

22 በዚያን ጊዜ ለሕዝቡ፣ “ሌሊት ዘብ በመጠበቅና ቀን ሥራ በመሥራት እንዲያገለግለን እያንዳንዱ ሰው ከነረዳቱ በኢየሩሳሌም ይቈይ” አልኋቸው።

23 እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ፣ ሰዎቼም ሆኑ ከእኔ ጋር ያሉት ጠባቂዎች ልብሳችንን አላወለቅንም፤ ለውሃ እንኳ በምንሄድበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን እንደ ያዘ ነበር።