ነህምያ 5:6-12 NASV

6 እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች በሰማሁ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣሁ፤

7 ከዚያም ነገሩን በሐሳቤ ካወጣሁ ካወረድሁ በኋላ፣ መኳንንቱንና ሹማምቱን ገሠጽኋቸው፤ “ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” አልኋቸውም። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ፤

8 ለአሕዛብ ተሽጠው የነበሩትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን ሁሉ ተቤዥተናቸዋል፤ አሁንም እናንተ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ፤ ይህም መልሰን እንድንቤዣቸው ለማድረግ ብቻ ነው!” አልኋቸው፤ እነርሱም የሚመልሱት አልነበራቸውምና ዝም አሉ።

9 ስለዚህ በመቀጠል እንዲህ አልሁ፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ትክክል አይደለም፤ የጠላቶቻችንን የአሕዛብን ስድብ ለማስወገድ የአምላካችንን መንገድ በፍርሀት መከተል አይገባችሁምን?

10 እኔ፣ ወንድሞቼና ሰዎቼም እንደዚሁ ለሕዝቡ ገንዘብና እህል አበድረናል፤ ዐራጣው ግን ያብቃ።

11 እርሻቸውን፣ የወይንና የወይራ ዘይት ተክል ቦታቸውንና ቤታቸውን በቶሎ መልሱላቸው፤ እንዲሁም የምታስከፍሏቸውን የገንዘቡን፣ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና ዘይት አንድ መቶኛ ዐራጣ መልሱላቸው”።

12 እነርሱም፣ “እንመልሳለን፤ ምንም ዐይነት ትርፍ አንጠይቃቸውም፤ እንዳልኸን እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱን ጠራኋቸው፤ መኳንንቱንና ሹማምቱም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አማልኋቸው።