ነህምያ 8:11-17 NASV

11 ሌዋውያኑም፣ “ይህች ቀን የተቀደሰች ስለሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ።

12 ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ።

13 ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ።

14 እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤

15 ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርስነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።”

16 ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ።

17 ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር።