ነህምያ 8:13-18 NASV

13 ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ።

14 እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤

15 ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርስነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።”

16 ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ።

17 ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር።

18 ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።