ነህምያ 8:5-11 NASV

5 ዕዝራም መጽሐፉን ከፈተ፤ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለ ነበረ፣ ሁሉም ያዩት ነበረ፣ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ።

6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።

7 ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ሰራብያ፣ ያሚን፣ ዓቁብ፣ ሳባታይ፣ ሆዲያ፣ መዕሤያ፣ ቆሊጣስ፣ ዓዛርያስ፣ ዮዛባት፣ ሐናን፣ ፌልያ ሕዝቡ በዚያው ቆመው እንዳሉ ሕጉን አስረዷቸው።

8 ሕዝቡ የሚነበበውን መረዳት እንዲችሉ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ካነበቡላቸው በኋላ ይተረጒሙላቸውና ይተነትኑላቸው ነበር።

9 ከዚያም አገረ ገዡ ነህምያ፣ ካህኑና ጸሓፊው ዕዝራ፣ ሕዝቡንም የሚያስተምሩት ሌዋውያን፣ “ይህች ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናት፤ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሏቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ያለቅሱ ነበር።

10 ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።

11 ሌዋውያኑም፣ “ይህች ቀን የተቀደሰች ስለሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ።