ነህምያ 9:1-7 NASV

1 በዚያኑ ወር ሃያ አራተኛ ቀን እስራኤላውያን ጾመው፣ ማቅ ለብሰው፣ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው በአንድነት ተሰበሰቡ።

2 የእስራኤላውያን ዘር የሆኑትም ራሳቸውን ከባዕዳን ሁሉ ለዩ። ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ።

3 በያሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ፤ የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ።

4 ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ ከናኒ፣ በመውጫ ደረጃዎች ላይ ቆሙ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅ ጮኹ።

5 ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ።“ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል።

6 አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል።

7 “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳው ያንዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ።