አሞጽ 8 NASV

የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት

1 ጌታ እግዚአብሔር ይህን አሳየኝ፤ እነሆ፤ የጎመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት ነበረ።

2 እርሱም፣ “አሞጽ ሆይ፤ ምን ታያለህ?” አለኝ። እኔም፣ “የጎመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት አያለሁ” አልሁ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ከእንግዲህም አልምራቸውም።”

3 ጌታ እግዚአብሔር፣ “በዚያ ቀን የቤተ መቅደሱ ዝማሬ ወደ ዋይታ ይለወጣል፤ እጅግ ብዙ የሆነ የሰው ሬሳ ወድቆ ይገኛል፤ ዝምታም ይሰፍናል” ይላል።

4 እናንት ችግረኞችን የምትረግጡ፣የምድሪቱንም ድኾች የምታጠፉ ይህን ስሙ፤

5 እንዲህም ትላላችሁ፤“መስፈሪያውን በማሳነስ፣ዋጋውን ከፍ በማድረግ፣በሐሰተኛ ሚዛን በማጭበርበር፣እህል እንድንሸጥ፣የወር መባቻ መቼ ያበቃል?ስንዴም ለገበያ እንድናቀርብ፣ሰንበት መቼ ያልፋል?”

6 ድኻውን በብር፣ችግረኛውንም በጥንድ ጫማ እንገዛለን፤ግርዱን እንኳ በስንዴ ዋጋ እንሸጣለን።”

7 እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ሲል ምሎአል፤ “እነርሱ ያደረጉትን ሁሉ ከቶ አልረሳም።

8 “በዚህ ነገር ምድር አትናወጥምን?በውስጧ የሚኖሩትስ ሁሉ አያለቅሱምን?የምድር ሁለመና እንደ ዐባይ ወንዝ ይነሣል፤እንደ ግብጽ ወንዝም ወደ ላይ ይፈናጠራል፤ተመልሶም ይወርዳል።”

9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በዚያ ቀን፣ ፀሐይ በቀትር እንድትጠልቅ አደርጋለሁ፤ምድርንም ደማቅ ብርሃን ሳለ በቀን አጨልማታለሁ።

10 ዓመት በዓላችሁን ወደ ልቅሶ፣ዝማሬአችሁንም ሁሉ ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ሁላችሁም ማቅ እንድትለብሱ፣ጠጒራችሁንም እንድትላጩ አደርጋለሁ፤ያን ጊዜ ለአንድያ ልጅ ሞት እንደሚለቀስበት፣ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።”

11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በምድር ላይ ረሐብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል፤ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ረሐብ እንጂ፣እንጀራን የመራብ ወይም ውሃን የመጠማት አይደለም።

12 ሰዎች እግዚአብሔርን ለመሻት፣ከባሕር ወደ ባሕር፣ከሰሜን ወደ ምሥራቅ ይንከራተታሉ፤ነገር ግን አያገኙትም።

13 “በዚያ ቀን፣“ቈነጃጅት ሴቶችና ብርቱዎች ጎልማሶች፣ከውሃ ጥም የተነሣ ይዝላሉ።

14 በሰማርያ ኀፍረት የሚምሉ፣ወይም፣ ‘ዳን ሆይ፤ ሕያው አምላክህን’ የሚሉ፣ወይም ‘ሕያው የቤርሳቤህ አምላክን’ ብለው የሚምሉ፣ዳግመኛ ላይነሡ፣ ለዘላለም ይወድቃሉ።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9