አስቴር 2:1-7 NASV

1 ከዚህ በኋላ ንጉሡ ጠረክሲስ ቊጣው ሲበርድለት አስጢንን፣ ያደረገችውን ነገርና በእርሷም ላይ ያስተላለፈውን ዐዋጅ ዐሰበ።

2 ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ የሚል ሐሳብ አቀረቡ፤ “ለንጉሡ ቈንጆ ልጃገረዶች ይፈለጉለት፤

3 እነዚህን ሁሉ ቈንጆ ልጃገረዶች በሱሳ ግንብ ወደሚገኘው ልዩ የሴቶች መኖሪያ ቦታ እንዲያመጡ፣ ንጉሡ በግዛቱ በሚገኙት አውራጃዎቹ ሁሉ ባለ ሥልጣኖችን ይሹም፤ እነርሱም የሴቶች የበላይ ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሄጌ ኀላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበትም እንክብካቤ ይደረግላቸው።

4 ከዚያም ንጉሡን ደስ የምታሰኘው ልጃገረድ በአስጢን ፈንታ ንግሥት ትሁን።” ምክሩ ንጉሡን ደስ አሰኘው፤ በተባለውም መሠረት አደረገ።

5 በዚህ ጊዜ ከብንያም ነገድ የቂስ ልጅ፣ የሰሜኢ ልጅ፣ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ በሱሳ ግንብ ይኖር ነበር፤

6 እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት አንዱ ነበር።

7 መርዶክዮስ አንዲት ሀደሳ የምትባል የአጎቱ ልጅ ነበረችው፤ አባትና እናት ስላልነበራት፣ ያሳደጋት እርሱ ነበር። አስቴር ተብላ የምትጠራው ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች። አባቷና እናቷ ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት።