1 ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ይገዛ በነበረው በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆነ፤
2 በዚያን ዘመን ንጉሡ ጠረክሲስ የገዛው በሱሳ ግንብ ባለው ንጉሣዊ ዙፋኑ ሆኖ ነበር።
3 እርሱም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ። በግብዣውም የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፣ መሳፍንትና የየአውራጃው መኳንንት ተገኝተው ነበር።
4 ለእነርሱም የመንግሥቱን ሰፊ ሀብት፣ የግርማውን ታላቅነትና ክብር አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሙሉ አሳያቸው።
5 እነዚህ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ንጉሡ በሱሳ ግንብ ለነበሩት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ዙሪያውን በአትክልት በተከበበው አደባባይ ሰባት ቀን የፈጀ ግብዣ አደረገ።
6 አደባባዩም ከነጭና ከሰማያዊ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤ እነርሱም የብር ቀለበት በተበጀላቸው፣ ከነጭ በፍታና ከሐምራዊ ቀለም በተሠሩ ገመዶች በዕብነ በረዱ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር። ነጭና ቀይ ቀለማት ተሰበጣጥረው በተነጠፉበት ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ ዐልጋዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከዕብነ በረድ፣ ቀስተ ደመና ከሚመስሉ ቀለሞችና ከሌሎች የከበሩ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ።
7 የወይን ጠጁም አንዱ ከሌላው ልዩ በሆነ የወርቅ ዋንጫ ይቀርብ ነበር፤ ከንጉሡም ልግስና የተነሣ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ የተትረፈረፈ ነበር።
8 ንጉሡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ያህል እንዲያቀርቡለት የወይን ጠጅ አሳላፊዎቹን ሁሉ አዝዞ ስለ ነበረ፣ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ ተስተናጋጅ እንዲጠጣ ተፈቅዶለት ነበር።
9 ንግሥት አስጢንም በንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት እንደዚሁ ለሴቶች ግብዣ አድርጋ ነበር።
10 በሰባተኛው ቀን ንጉሥ ጠረክሲስ ከወይን ጠጁ የተነሣ ደስ ስለ ተሰኘ፣ አገልጋዮቹ የሆኑትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፣ ባዛንን፣ ሐርቦናን፣ ገበታን፣ ዘቶልያንን፣ ዜታርንና ከርከስን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤
11 ይኸውም ንግሥት አስጢን የደስ ደስ ያላት ነበረችና ውበቷ ለሕዝቡና ለመኳንንቱ እንዲታይ ዘውዷን ጭና ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነበር።
12 አገልጋዮቹ የንጉሡን ትእዛዝ በነገሯት ጊዜ ግን፣ ንግሥት አስጢን መሄድ አልፈለገችም። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቈጣ፤ እጅግም ተናደደ።
13 ሕግንና ፍትሕን በተመለከተ የሊቃውንቱን ምክር መጠየቅ በንጉሥ ዘንድ የተለመደ ነበርና፣ ስለ ዘመናት ሁኔታ ዕውቀት ካላቸው ጠቢባን ጋር ተነጋገረበት፤
14 እነዚህ አርቄስዮስ፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሺሽ፣ ሜሬስ፣ ማሌሴዓር፣ ምሙካ የተባሉ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት በንጉሡ ዘንድ የተለየ ስፍራና በመንግሥቱም አመራር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ነበሩ።
15 ንጉሡም፣ “በጃንደረቦቹ በኩል የተላከባትን የንጉሥ ጠረክሲስን ትእዛዝ ስላልፈጸመች፣ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቃቸው።
16 ከዚያም ምሙካ በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን፣ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ጭምር ነው።
17 ይህ የንግሥቲቱ አድራጎት በሌሎቹ ሁሉ ዘንድ ስለሚሰማ፣ ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ‘ንጉሥ ጠረክሲስ ንግሥት አስጢን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያዛትም፣ እርሷ ግን መሄድ አልፈለገችም’ ይላሉ።
18 በዚህች በዛሬዪቱም ዕለት የንግሥቲቱን አድራጎት የሰሙ የፋርስና የሜዶን መኳንንት ሚስቶች፣ ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሊመልሱ ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ማብቂያ የሌለው ንቀትና ጠብ ይፈጠራል።
19 “ስለዚህ ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ ጠረክሲስ ዘንድ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ እንዳትገባ ንጉሣዊ ዐዋጅ ይውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ይጻፍ፤ እንዲሁም ንጉሡ የእቴጌነቷን ክብር ከእርሷ ለምትሻል ለሌላዪቱ ይስጥ።
20 ከዚያም የንጉሡ ዐዋጅ በሰፊው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉት ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።”
21 ንጉሡና መኳንንቱ ሁሉ በዚህ ምክር ተደሰቱ፤ ንጉሡም ምሙካ ያቀረበውን ሐሳብ በሥራ ላይ አዋለው።
22 እያንዳንዱ ሰው በራሱ ቤተ ሰብ ላይ ገዥ እንዲሆን መልእክት አስተላለፈ፤ መልእክቱም ለየአውራጃዎቹ በየራሳቸው ጽሑፍና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ ተጽፎ በግዛቱ ሁሉ ተበተነ።