አስቴር 3:8-14 NASV

8 ከዚያም ሐማ ንጉሥ ጠረክሲስን እንዲህ አለው፤ “በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተሠራጭቶና ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ልማድ ያለውና የንጉሡንም ሕግ የማይታዘዝ ነው፤ ታዲያ ይህን ሕዝብ ዝም ማለቱ ለንጉሡ አይበጅም።

9 ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ እነርሱን ለማጥፋት ዐዋጅ ይውጣ፤ እኔም ይህን ተግባር ለሚፈጽሙ ሰዎች የሚውል ዐሥር ሺህ መክሊት ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት አስገባለሁ።”

10 ስለዚህ ንጉሡ የቀለበት ማኅተሙን ከጣቱ አውልቆ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለአጋጋዊው ለሐማዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው።

11 ንጉሡም ሐማን፣ “ገንዘቡን እዚያው ያዘው፤ ሕዝቡንም እንዳሻህ አድርገው” አለው።

12 ከዚያም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሓፊዎች ተጠሩ። እነርሱም የሐማን ትእዛዝ በሙሉ በየአውራጃው ፊደልና በየሕዝቡ ቋንቋ፣ ለንጉሡ እንደራሴዎች፣ ለልዩ ልዩ አውራጃ ገዦችና ለልዩ ልዩ ሕዝቦች መኳንንት ጻፉ። ይህም የተጻፈው በራሱ በንጉሡ ጠረክሲስ ስም ሲሆን፣ የታተመውም በራሱ ማኅተም ነበር።

13 አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ሴትና ሕፃን ሳይባል አይሁድ ሁሉ በዚያኑ ዕለት እንዲጠፉ፣ እንዲገደሉና እንዲደመሰሱ፣ ሀብታቸውም እንዲዘረፍ ደብዳቤ ለንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ በመልእክተኞች እጅ ተላከ።

14 ለእያንዳንዱም አውራጃ ሕዝብ እንዲታወቅ፣ እነርሱም ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የዋናው ዐዋጅ ቅጅ ሕግ እንዲወጣና ወደ እያንዳንዱም አውራጃ እንዲላክ ተደረገ።