1 በዚያኑ ዕለት ንጉሥ ጠረክሲስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ንብረት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤ አስቴርም መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበር፣ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀረበ።
2 ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ባለ ማኅተም ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ቤት ንብረት ላይ ሾመችው።
3 አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ ልመናዋን እንደ ገና አቀረበች። አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ክፉ ሤራ እንዲሽር ለመነችው።
4 ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች።