አስቴር 8:1-6 NASV

1 በዚያኑ ዕለት ንጉሥ ጠረክሲስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ንብረት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤ አስቴርም መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበር፣ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀረበ።

2 ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ባለ ማኅተም ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ቤት ንብረት ላይ ሾመችው።

3 አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ ልመናዋን እንደ ገና አቀረበች። አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ክፉ ሤራ እንዲሽር ለመነችው።

4 ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች።

5 እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጉዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሰኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ።

6 በሕዝቤ ላይ መዐት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የቤተ ሰቤንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?”