አስቴር 9:18-24 NASV

18 በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ግን በዐሥራ ሦስተኛውና በዐሥራ አራተኛው ቀን ተሰብስበው ነበር፤ ከዚያም በዐሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፉ፤ ዕለቱንም የተድላና የደስታ ቀን አድርገው ዋሉ።

19 በየመንደሩ የሚኖሩ የገጠር አይሁድ፣ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛ ቀን የተድላና የደስታ፣ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚለዋወጡበት ቀን አድርገው የሚያከብሩት ከዚሁ የተነሣ ነው።

20 መርዶክዮስ የተፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ጻፈ፤ ደብዳቤ አዘጋጅቶም በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት አይሁድ ሁሉ ላከ፤

21 የላከውም የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በየዐመቱ እንዲያከብሩ ነው፤

22 የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።

23 ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤

24 ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር።