4 ከዚያም የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ።
5 ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ዕቅዶቻቸውን የሚያሰናክሉ መካሪዎችን በገንዘብ ገዙባቸው።
6 በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው።
7 በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትሪዳጡ፣ ጣብኤልና ተባባሪዎቹ ወደ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤው የተጻፈው በአረማይስጥ ፊደል፣ በአረማይስጥ ቋንቋ ነበረ።
8 አገረ ገዡ ሬሁምና ጸሓፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፤
9 ደብዳቤው የተጻፈው፣ ከአገረ ገዡ ሬሁም፣ ከጸሓፊው ሲምሳይ በትሪፖሊስ፣ በፋርስ፣ በአርክ፣ በባቢሎን፣ እንዲሁም በሱሳ ማለትም በኤላማውያን ላይ ዳኞችና ገዦች ከሆኑት ከተባባሪዎቻቸው፣
10 ደግሞም ታላቁና ኀያሉ አስናፈር አፍልሶ በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ሌሎች ሕዝቦች ነው።