1 እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ መሪዎቹ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፤ “ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ ከጎረቤቶቻቸው ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኢያቡሳውያን፣ ከአሞናውያን ርኵሰት ራሳቸውን አልለዩም።
2 ሴቶቻቸውን ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ በደል ዋነኛ የሆኑትም መሪዎቹና ሹማምቱ ናቸው።”
3 እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ፣ መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራሴን ጠጒርና ጢሜን ነጨሁ፤ እጅግ ደንግጬም ተቀመጥሁ።
4 በደል ከፈጸሙት ምርኮኞች የተነሣም በእስራኤል አምላክ ቃል የተንቀጠቀጡት ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ እጅግ እንደ ደነገጥሁ በዚያው ተቀመጥሁ።
5 ከዚያም፣ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ የተቀደደውን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን እንደ ለበስሁ በሐዘን ከተቀመጥሁበት ተነሣሁ፤ በጒልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን በመዘርጋት፣
6 እንዲህ ስል ጸለይሁ፤“አምላኬ ሆይ፤ ኀጢአታችን ከራሳችን በላይ ሆኖአል፤ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሶአል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ፤ እጅግም ፈራሁ።
7 ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በደላችን ታላቅ ነው። ከኀጢአታችንም የተነሣ፣ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ እኛም ሆንን፣ ነገሥታቶቻችንና ካህናቶቻችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣ ለምርኮ፣ ለብዝበዛና ለውርደት ተዳርገናል።
8 “አሁን ግን እግዚአብሔር አምላካችን ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፣ በመቅደሱም ውስጥ ጽኑ ስፍራ ይሰጠን ዘንድ፣ ለጥቂት ጊዜ ቸርነቱን አሳይቶናል፤ ስለዚህ አምላካችን ለዐይናችን ብርሃን ሰጠን፤ በባርነትም ሳለን ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት ሰጠን።
9 ባሮች ብንሆንም፣ አምላካችን ግን ባሮች ሆነን እንድንቀር አልተወንም፤ ነገር ግን በፋርስ ነገሥታት ፊት ቸርነቱን አሳየን፤ የአምላካችንን ቤት እንደ ገና እንድንሠራና ፍርስራሾቿን እንድንጠግን አዲስ ሕይወት ሰጠን፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የመከላከያ ቅጥር ሰጠን።
10 “አሁን ግን አምላካችን ሆይ፤ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዞችህን አቃለናልና፤
11 ያቃለልነውም በባሮችህ በነቢያት አማካይነት፣ ‘ለመውረስ የምትገቡባት ምድር በሕዝቦቿ ርኵሰት ተበክላለች፤ ከዳር እስከ ዳርም በአስጸያፊ ድርጊታቸውና በርኵሰታቸው ተሞልታለች፣
12 ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ። ብርቱዎች እንድትሆኑ፣ የምድሪቱን መልካም ነገር እንድትበሉና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት እንድታወርሱ ከእነርሱ ጋር ምንም ዐይነት ውል አታድርጉ’ ብለህ የሰጠኸውን ትእዛዝ ነው።
13 “ይህ ሁሉ የደረሰብን በክፉ ሥራችንና በብዙ በደላችን ምክንያት ነው፤ አምላካችን ሆይ፤ አንተ ግን እንደ በደላችን ብዛት አልቀጣኸንም፤ ይልቁንም ቅሬታን ተውህልን።
14 ታዲያ ትእዛዞችህን እንደ ገና ተላልፈን እንዲህ ያለውን አስጸያፊ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሕዝቦች ጋር መጋባት ተገቢ ነውን? አንተስ ቅሬታ እስከማይኖር ወይም አንድም ሰው እስከማይድን ድረስ ተቈጥተህ አታጠፋንምን?
15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛም በዚህ ዕለት ተርፈን በሕይወት አለን። እነሆ፣ በፊትህ ከነበደላችን ቀርበናል፤ ከበደላችን የተነሣ ግን በፊትህ ሊቆም የሚችል ማንም የለም።