ዕዝራ 10 NASV

ሕዝቡ ኀጢአቱን ተናዘዘ

1 ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ወድቆ በሚጸልይበት፣ በሚናዘዝበትና በሚያለቅስበት ጊዜ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚገኙበት እጅግ ብዙ የእስራኤል ማኅበር በዙሪያው ተሰበሰበ፤ እነርሱም እንደዚሁ አምርረው አለቀሱ።

2 ከዚያም ከኤላም ዘሮች አንዱ የሆነው የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፤ “በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ፣ ባዕዳን ሴቶችን በማግባታችን ለአምላካችን ታማኞች ሆነን አልተገኘንም፤ ይህም ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ።

3 አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም።

4 ዕዝራ፣ ነገሩ በእጅህ ነው፤ ተነሥ! እኛም እንደግፍሃለን፤ በርትተህም፤ አድርገው።”

5 ዕዝራም ተነሥቶ ዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ ሌዋውያንና እስራኤል ሁሉ የቀረበውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ አስማላቸው፤ እነርሱም ማሉ።

6 ከዚያም ዕዝራ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ክፍል ገባ፤ ምርኮኞቹ ታማኞች ሆነው ባለ መገኘታቸው ያለቅስ ነበር፤ በዚያም ምግብ አልቀመሰም፤ ውሃም አልጠጣም።

7 ከዚያም ምርኮኞቹ ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ፤

8 ዐዋጁም በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንም ሰው በሹማምቱና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፣ ራሱም ከምርኮኞቹ ጉባኤ እንዲወገድ የሚያዝ ነበር።

9 ስለዚህ በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ በዘጠነኛው ወር በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ስለ ወቅቱ ጒዳይና ስለ ከባዱ ዝናብ በመጨነቅ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀምጠው ነበር።

10 ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ታማኞች አልነበራችሁም፤ በእስራኤል በደል ላይ በደል በመጨመር ባዕዳን ሴቶችን አገባችሁ።

11 አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ ፈቃዱን ፈጽሙ፤ በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ተለዩ።”

12 ጉባኤውም ሁሉ እንዲህ ሲሉ በታላቅ ድምፅ መለሱ፤ “እውነት ብለሃል፤ ያልኸውን መፈጸም ይገባናል።

13 ይሁን እንጂ በዚህ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው፤ ወቅቱም ክረምት ነው፤ ስለዚህ ውጭ መቆም አንችልም፤ ከዚህም በላይ በዚህ ነገር ብዙ ኀጢአት ስለ ሠራን፣ ይህ ጒዳይ በአንድና በሁለት ቀን የሚያልቅ አይደለም።

14 ስለዚህ ሹሞቻችን በማኅበሩ ሁሉ ምትክ መደረግ ያለበትን ያድርጉ። ከዚያም በዚህ የተነሣ የመጣው የአምላካችን ብርቱ ቊጣ ከእኛ እስኪመለስ ድረስ፣ በየከተሞቻችን ያሉ ባዕዳን ሴቶችን ያገቡ ሁሉ በየከተማው ካሉት ሽማግሌዎችና ዳኞች ጋር በተወሰነው ቀን ይምጡ።”

15 ይህንንም ነገር የተቃወሙት ከሜሱላምና ከሌዋዊው ከሳባታይ ድጋፍ ያገኙት የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሕዝያ ብቻ ናቸው።

16 ስለዚህ ምርኮኞቹ እንደ ተባለው አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራም ከእያንዳንዱ የቤተ ሰብ ምድብ አንዳንድ የቤተ ሰብ ኀላፊ የሆነ ሰው መረጠ፤ ሁሉም በየስማቸው ተመዘገቡ። ከዚያም በዐሥረኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ጒዳዩን ለመመርመር ተቀመጡ፤

17 በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ባዕዳን ሴቶችን ያገቡትን ወንዶች ሁሉ አጣርተው ጨረሱ።

ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡት ሰዎች

18 ከካህናት ዘሮች መካከል ባዕዳን ሴቶችን ያገቡት ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፤ከኢዮሴዴቅ ልጅ ከኢያሱ ዘሮችና ከወንድሞቹ መካከል፤ መዕሤያ፣ አልዓዛር፣ ያሪብና ጎዶልያስ።

19 እነዚህ ሁሉ ሚስቶቻቸውን ለመፍታት ቃል በመግባት እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም እያንዳንዳቸው ከመንጋው አንዳንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ።

20 ከኢሜር ዘሮች፤አናኒና ዝባድያ።

21 ከካሪም ዘሮች፤መዕሤያ፣ ኤልያስ፣ ሸማያ፣ ይሒኤልና ዖዝያ።

22 ከፋስኩር ዘሮች፤ኤልዮዔናይ፣ መዕሤያ፣ ይስማኤል፣ ናትናኤል፣ ዮዛባትና ኤልዓሣ።

23 ከሌዋውያኑም መካከል፤ዮዛባት፣ ሰሜኢ፣ ቆሊጣስ የሚባል ቆልያ፣ ፈታያ፣ ይሁዳ፣ አልዓዛር።

24 ከመዘምራኑም መካከል፤ኤልያሴብ።ከበር ጠባቂቹም፣ሰሎም፣ ጤሌም፣ ኡሪ።

25 ከሌሎቹ እስራኤላውያን መካከል፤ከፋሮስ ዘሮች፤ ራምያ፣ ይዝያ፣ መልክያ፣ሚያሚን፣ አልዓዛር፣ መልክያና በናያስ።

26 ከኤላም ዘሮች፤መታንያ፣ ዘካርያስ፣ ይሒኤል፣ አብዲ፣ ይሬሞትና ኤልያ።

27 ከዛቱዕ ዘሮች፤ዒሊዮዔናይ፣ ኢልያሴብ፣ መታንያ፣ ይሬሞት፣ ዛባድና ዓዚዛ።

28 ከቤባይ ዘሮች፤ይሆሐናን፣ ሐናንያ፣ ዛባይና አጥላይ።

29 ከባኒ ዘሮች፤ሜሱላም፣ መሉክ፣ ዓዳያ፣ ያሱብ፣ ሸዓልና ራሞት።

30 ከፈሐት ሞዓብ ዘሮች፤ዓድና፣ ክላል፣ በናያስ፣ መዕሤያ፣ መታንያ፣ ባስልኤል፣ ቢንዊና ምናሴ።

31 ከካሪም ዘሮች፤አልዓዛር፣ ይሺያ፣ መልክያ፣ ሸማያ፣ ስምዖን፣

32 ብንያም፣ መሉክና ሰማራያ።

33 ከሐሱም ዘሮች፤መትናይ፣ መተታ፣ ዛባድ፣ ኤሊፋላት፣ ይሬማይ፣ ምናሴና ሰሜኢ።

34 ከባኒ ዘሮች፤መዕዳይ፣ ዓምራም፣ ኡኤል፣

35 በናያስ፣ ቤድያ፣ ኬልቅያ፣

36 ወንያ፣ ሜሪሞት፣ ኤልያሴብ፣

37 መታንያ፣ መትናይና የዕሡ።

38 ከቢንዊ ዘሮች፤ሰሜኢ፣

39 ሰሌምያ፣ ናታን፣ ዓዳያ፣

40 መክነድባይ፣ ሴሴይ፣ ሸራይ፣

41 ኤዝርኤል፣ሰሌምያ፣ ሰማራያ፣

42 ሰሎም፣ አማርያና ዮሴፍ።

43 ከናባው ዘሮች፤ይዒኤል፣ መቲትያ፣ ዛባድ፣ ዘቢና፣ ያዳይ፣ ኢዮኤልና በናያስ።

44 እነዚህ ሁሉ ባዕዳን ሴቶችን ያገቡ ናቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹ ከእነዚህ ሴቶች ልጆችን ወልደው ነበር።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10